ከመጻሕፍት ዓለም (Ethio Books World)

አንዴ ስመጥሩ ነው ተብሎ ወደሚነገርለት ላውንደሪ 5 ሸሚዞች ወስጄ ሰጠሁ። ሸሚዞቹ ውድና አንዴም ያልታጠቡ ነበሩ። በቀጠሮው ቀን ስሄድ አራቱ ሸሚዞች መጥፋታቸውን ተነገረኝ። ምን እንደሚበጀኝ ብጠይቅ፣ “የማሳጠቢያው አስር እጥፍ ይከፈልሃል” ተባልኩ። 7.50 መሆኑ ነው። ሌላ ምርጫ ስለሌለኝ እሱኑ ለመቀበል ብስማማም፣ “ባለቤቱ ለጥቂት ወጣ አሉ። ጉዳዩን የምታውቀው ሰራተኛ ወልዳ ተኝታለች፣ ለጊዜው ቲኬቱን ለማግኘት አልቻልንም።” በማለት ሲያመላልሱኝ ከርመው እግሬ ስለቀጠነ ሸሚዞቼ ቀልጠው ቀሩ።

የደረቅ እጥበት ጣጣ
ከእሸቱ ተፈራ

እፍታ (መቶ ትረካዎች፥ ቅፅ አምስት) | አዘጋጅና አርታኢ ተስፋዬ ገብረአብ | 1993 ታተመ | ገጽ 422-423

[…] ሌት ከዋክብቱ እንደፀደይ
አጥለቅልቆን በቀይ አደይ
ሰማዩ ሥጋጃ አጥልቆ
ተሽለምልሞ አንጸባርቆ
ፈክቶ፥ አሸብርቆ ደምቆ
በአዝመራ፥ በአጥቢያ ዐፀድ ሰፍኖ
የዓደይ አዝርዕት ተከሽኖ
በዕንቁጣጣሽ ሰብል ታጥኖ
ኢዮሃ አበባዬ ሆኖ፥
ጨረቃዋ ከቆባዋ፥ ከሽልምልሚት እምቡጧ
ጧ ብላ ከሰንኮፈንዋ፥ ተንዠርግጎ የእንኮይ ቡጧ፥
ድንግል ጽጌ-ረዳ ፈልቃ
ፍልቅልቂት ድምቡል ቦቃ …
ተንሠራፍታ የአበባ ጮርቃ፥
ታድያን ብሌኑ የጠጠረ
ባሕረ-ሃሳቡ የከረረ
የውበት ዓይኑ የታወረ
ልበ-ሕሊናው የሰለለ
አይ፥ አበባ አይደለም አለ፤
አይ፥ እሳት አይደለም አለ፤
ያልታደለ። …
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥ እሳት አደል ብሎ ካደ
እቶን ባይኑ እየነደደ።
ከዋክብቱ እንደ ችቦ
በነበልባል ወርቀ ዘቦ
ከፅንፍ ፅንፍ አውለብልቦ
ደመራው እየተመመ
እየፋመ እየጋመ
ደመና እንደንዳድ ሲነድ
መንጸባርቅ ሰደድ ሲወርድ፥
በራሪ ኮከብ ተኩሶ
በአድማሳት እሳት ለኩሶ…
ይኸ እንደኔና እንዳንቺው፥ የውበት ዓይኑ የሰለለ
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥ እሳት እኮ አይደለም አለ፥
ያልታደለ። …

… ይቅር ብቻ አንናገርም፥
እኔና አንቺ አንወያይም፤
ለውይይት አልታደልንም
እንዲያው ዝም፥ እንዲያው ዝም … ዝም።
አበባ አንሆን ወይ እሳት
ተጠምደን በምኞት ቅጣት
ሰመመን ባጫረው መዓት
ዕድሜአችንን እንዳማጥናት፤ …

እሳት አንሆን ወይ አበባ
በሕቅ እንቅ ስንባባ
ባከነች ልጅነታችን፥ እየቃተትን ስናነባ
ሳንፈጠር በሞትንባት
ሳናብብ በረገፍንባት
ሳንጠና ባረጀንባት
አበባ ወይንም እሳት፥ መሆኑን ብቻ አጣንባት።

እሳት ወይ አበባ | ከጸጋዬ ገብረ መድኅን | 1960/1999 ዓ.ም ታተመ | ገጽ 152-154

ዘነበ ወላ፦ “በአንተ የወጣትነት ጊዜ በአማርኛ ሃሳብን መግለፅ አይቻልም ብላችሁ አንተም ሆንክ ጓደኞችህ በእንግሊዝኛ መጻፍ የወሰናችሁበት ወቅት እንደነበረ ይነገራል። በኋላ ደግሞ ወደ አማርኛው ተመልሰህ ድንቅ ፀሐፊ ወጣህ። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ብትገልፅልኝ?”

ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፦ “በወጣትነቴ አማርኛ በምፈልገው መልኩ ሀሳብን መግለፅ አያስችልም የሚል እምነት ነበረኝ። በዚህም ላይ ያስተማሩን እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች መሆናቸውን አትርሣ። እኛ አናውቅም እንጂ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወጣቱን ትውልድ በቅኝ አገዛዝ ጥበባቸው ይዘውናል። በኋላ ዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስን” ጻፈ። እኔ ሣነበው በአማርኛ መፃፍ እንደሚቻል ገባኝ። ስለዚህ በእንግሊዝኛ የመፃፍ ሀሳቤን ተውኩት። በወቅቱ አስታውሳለሁ “ሌቱም አይነጋልኝን” በእንግሊዘኛ መጻፍ ጀምሬው ነበር። 65 የተተየበ ገጽ ላይ አቆምኩት። … አፍሪካውያን ደራሲያን ሀገራቸው የእንግሊዝ ወይም የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስለነበረ በገዢው ቋንቋ ነው እያነበቡ ያደጉትና የሚፅፉት። እኛ ሀገር እንደዚያ ዓይነት ባሕል አልነበረም። አብዛኞቻችን የምንጽፈው በአማርኛ ነው። በእንግሊዝኛ የምንጽፍ ጥቂት ነን።

ማስታወሻ (ስብሐት ገብረእግዚአብሔር) | ከዘነበ ወላ | 1993 ዓ.ም ታተመ | ገጽ 238