ከመጻሕፍት ዓለም (Ethio Books World)

ማሞ ቂሎ

“ተማር ልጄ” ሲሉት አይሰማም አይሰማም
“ሥራ ልጄ” ሲሉት አይሰማም አይሰማም
ያርባ አመቱ ህጻን ካልመቱት አይሰማም
ካልመቱት አይሰማም ካልቆነጠጡት
ወይ ካላስፈራሩት በቃላት አለንጋ በቃላት ብትር
ሥራውን አይሰራ ትምህርት አይማር።

እድሜው ረጅም ነው ሰላሳ አርባ ሃምሳ
ልምድ ያላስተማረው ያምሮ ኮሳሳ
ሥራውን አይሰራ
ወሬ እየፈተለ
ወሬ እያደራ።

ታይፑ አይመታ
ጭቃው አይቦካ
መንገዱ አይሰራ
በልግም ለገማ።

ፊርማው አይፈረም
ሒሳብ አይቆረጥ
ቤቱ አይጠረግ
በኪስ ኪስ ተብሎ
ኪሱ ሳይታሸግ።

ህጻን ያርባ አመቱ ሥራውን አይሰራ
ካላስደነገጡት በቃላት አለንጋ
በብትር ባርጩሜ ባርጩሜ ባለንጋ።

አያ ጎሽሜ | ከፈቃደ አዘዘ | 1973

እፍታ | ቅጽ አመስት (መቶ  ትረካዎች) | አዘጋጅና አርታኢ ተስፋዬ ገብረአብ | ታተመ 1993 

ባሥራ ዘጠኝ መቶ አሥራ አራት ዓመት
በሚያዚያ አስራ ስድስት ቀኑም ሰኞለት
ባትላንቲክ አቋርጠን ስናልፍ አሰብሁት።
ልብ ያለው ይመልከት ይኸነን ጽፈት
ልጅ ያወራው ነገር አይቀርም ትንቢት።

…ሶስት ሆነን ስንሄድ ሰዎች አይተውን
የት ትሄዱ ብለው ጠርተው ጠየቁን።
እኛም ምላሽ ሰጠን እንደዚህ ብለን
ትምሕርት ፍለጋ ወደ አሜሪካን።
የየት ናችሁ ቢሉን የኢትዮጵያዊያን።
እጅግ ተደነቁ በነገራችን
ለትምርት ተልከን በመሄዳችን።
ጥርስ ፈልቀቅ አርገው አሉ ይኸነን
እናንተም ለትምርት አሰባችሁን።
እኛም ተደነቅን ይኸን ከሰማን
ያገራችን ነገር እያሳዘነን።
ባላየሁ የሚሻል የሚበልጠኝን
አሁን ምን አባቴ ልሰራ ይሆን።
አላሰብኩም ነበር እኔ እንዲህ ነው ብዬ
ማየት ያስጨንቃል ዋ ሆዬ ዋ ሆዬ።

…በመንገድም ሳለሁ አሰብሁ ይኸነን
የኢትዮጵያ ማማር የድኅነቷን
ረዳትና አገልጋይ ያለማግኘቷን።

…እንማር እናጥና እንወቅ በብዙ
የሰው አገር ሰዎች መጥተው እንዳይገዙ።
ብናስብ ብንማር በሁሉ ተግተን
ሳናውቀው አንቀርም ሰው የሰራውን።
መማር ይገባናል የሚቻለነን
ካልተማርንስ ሄደች አገርም የለን።
ሳትሄድ እንማር ኋላ እንዳይቆጨን
ባናውቃት ነው እንጂ አገራችነን
ወርቅና ብር ናት ወጣ ገባዋን።
አሻግረው ያዋታል መርምረው ውስጧን
ውበትና ጣሟን አውቀው ምሥጢሯን።
ቢያውብኝ አልወድም ለምለም አገሬን
እማራለሁ እንጂ የሚሻለውን።

…የኢትዮጵያ ልጆች ስሙኝ ልንገራችሁ
ከትምርት በተቀር ሌላም አይበልጧችሁ።
ዓይን አላነሰ አልጨለመባችሁ
እጅ ጠፋ አይባል ግራ ቀኝ አላችሁ
አንደበት አይባል ደማም ነገራችሁ
ራስ የለ አይባል ሙሉ ሰሌዳችሁ
ልብ የለ እንዳይባል ዋ አደፋፈራችሁ
አእምሮ እንዳይባል ወደ ቁምነገራችሁ
አሥራሁለት አካል በሙሉ ሰጣችሁ
አስተማሪ ብቻ እግዜር በደላችሁ
በሃይማኖትማ ማንም አያኽላችሁ
ምን አባቴ ልሁን አነሰ ዕውቀታችሁ
የዕውቀት አስተማሪ እግዚአብሔር ይስጣችሁ
እንዴሁም አትቀሩ ወንድሞቼ አይዟችሁ።

በዚህ ሁሉ ነገር ይቅርታ ስጡኝ
አላደግሁም ገና የዕውቀት ሕፃን ነኝ
እንዲያው ጻፍኩት እንጂ ትዝ ብትሉኝ
እሱም ልክ አልሆነ መርከብ ነቅንቆኝ
ጨርሳችሁ እዩት ጥፋትም ቢገኝ።

ለኢትዮጵያ ልጆች ማሳሰቢያ | ከመላኩ በየን | ታተመ 1915 | ገጽ 12-17

ሹመት።

(ውስጠቀ፡ ግጥም፡)

ካላጨበጨቡ፡
ወይ፡ ካልቸበቸቡ፡
ወይም፡ ካልሰረቱ፡
ወይ፡ ካላሰረቱ፡
ወይ፡ ካላሳበቱ፡
ማ፡ ለማ፡ ያቀምሳል፡ ከዚያ፡ ከሱረቱ?

ባሻ አሸብር በአሜሪካ (የፖለቲካ እስረኛ ግጥሞች) | ከመንግስቱ ለማ | ታተመ 1967 | ገጽ 5