ዘነበ ወላ፦ “በአንተ የወጣትነት ጊዜ በአማርኛ ሃሳብን መግለፅ አይቻልም ብላችሁ አንተም ሆንክ ጓደኞችህ በእንግሊዝኛ መጻፍ የወሰናችሁበት ወቅት እንደነበረ ይነገራል። በኋላ ደግሞ ወደ አማርኛው ተመልሰህ ድንቅ ፀሐፊ ወጣህ። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ብትገልፅልኝ?”
ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፦ “በወጣትነቴ አማርኛ በምፈልገው መልኩ ሀሳብን መግለፅ አያስችልም የሚል እምነት ነበረኝ። በዚህም ላይ ያስተማሩን እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች መሆናቸውን አትርሣ። እኛ አናውቅም እንጂ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወጣቱን ትውልድ በቅኝ አገዛዝ ጥበባቸው ይዘውናል። በኋላ ዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስን” ጻፈ። እኔ ሣነበው በአማርኛ መፃፍ እንደሚቻል ገባኝ። ስለዚህ በእንግሊዝኛ የመፃፍ ሀሳቤን ተውኩት። በወቅቱ አስታውሳለሁ “ሌቱም አይነጋልኝን” በእንግሊዘኛ መጻፍ ጀምሬው ነበር። 65 የተተየበ ገጽ ላይ አቆምኩት። … አፍሪካውያን ደራሲያን ሀገራቸው የእንግሊዝ ወይም የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስለነበረ በገዢው ቋንቋ ነው እያነበቡ ያደጉትና የሚፅፉት። እኛ ሀገር እንደዚያ ዓይነት ባሕል አልነበረም። አብዛኞቻችን የምንጽፈው በአማርኛ ነው። በእንግሊዝኛ የምንጽፍ ጥቂት ነን።
“
| — |
ማስታወሻ (ስብሐት ገብረእግዚአብሔር) | ከዘነበ ወላ | 1993 ዓ.ም ታተመ | ገጽ 238
|
ከአሥመራ ወደ ምፅዋ ለሚወርድ መንገደኛ ምፅዋ ከመድረሱ ሃያ ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀረው፥ ተድአሊ የተባለችውን ቀበሌ ያገኛል። ገና ከጊንዳዕ በታች የሚገኘውን ገደላ ገደል ወርዶ የዳማስን ሜዳ እንዳለፈ የሚጋረፈው የቆላ ሐሩር ይቀበለዋል። …
ከሜድትራኒያን አከባቢ የሚነሣው የክረምት ጊዜ በቀይ ባሕር አካባቢ ያሉትን አገሮች ከልሎ በሚወስድበት ወቅት ቃጠሎውና ደረቁ አከባቢ ወደ ለምለምነት ስለሚለወጥ ከጊንዳዕ ጀምሮ እስከ ምፅዋ ያለው ወረዳም ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ መጨረሻ ድረስ የሚታይበት ውበት፥ የሚገኝበት የመሬት ፍሬና የአየር ለውጥ የማይጠገብ ነው።
ራስ አሉላም ከጊንዳዕ ወደ ሰሐጢ የወረዱት በጥር አጋማሽ ላይ ነበር። የአየሩ ጠባይ አልፎ አልፎ ዝናብ የሚጥል መሬቱ በልምላሜ የተሸፈነ ነበር። …
ራስ አሉላ፥ በተፈጥሮአቸው ከወረሱት ጸጋ የጦር ስልት ሲያወጡ ወይም ጦርነት ለመግጠም ሲያስቡ የአየር ጠባይንም በቅድሚያ ለማወቅ የሚያደርጉት ጥረት ነው። ሠራዊታቸው በሐሩር፥ በጨለማ፥ በወባ፥ በኃይለኛ ዝናብ ጎርፍና ጉም እንዳይጠመድባቸው እጅግ ይጠነቀቁ ነበር። …
…ራስ አሉላ ከንጋቱ ላይ ሰሐጢ አጠገብ ደርሰው የወታደራቸውን አሰላለፍ በዝርዝር ተመለከቱ። … ፀሐይ ስትወጣ ከጀርባቸው እንድትሆን አደረጉና ጦርነቱን ጀመሩ። … የመድፍና የጠመንጃው ተኩስ ቀረና ውጊያ በጨበጣ ሆነ። ራሳቸው ራስ አሉላ ከፈረሳቸው ወርደው እንደ ተራ ወታደር በተድአሊ ወንዝና ዳገት እየዘለሉ ከጠላት ጦር ጋር ተደባለቁ። … ጉራዕ ላይ በግብፅ ኩፊት ላይ በድርቡሹ አንገት ላይ በደም ያጠቡትን ጎራዴያቸውን መዘዙና የጣልያኑ ጦር መከላከያ ለመሥራት ሲጣደፍበት ወደነበረው ቁብታ ወጥተው ለሸለሹት። …
[…አቀንቃኝ…] ኪዳኔ መብራቱም፥
“ጎራው ተማሙቋል መሬት ተደባልቋል፤
ነጩ ክምር ፈርሶ ምስቅልቅሉ ወጥቷል።
…ሚስትህ ምነው ባየች በሰማች እናትህ፤
በአሉላ ጎራዴ ሲበጠስ አንገትህ።
የነማን አገር ነው ብለው ሳይጠይቁ፤
አገር የደፈሩ እነሆ ወደቁ።
ምነው በጠየቁ የግብፅን ወታደር፤
ምነው በጠየቁት የድርቡሽ ወታደር፤
እንደማይደፈር ያባነጋ መንደር።”
እያለ አቅራራ።
“
| — |
አሉላ አባ ነጋ | ከማሞ ውድነህ | 1979 ዓ.ም ታተመ | ገጽ 237-241
|
ታንጉት የኖረችው በሕፃንነቷ በገጠር፥ በኋላም፥ ባልዋ በዘመተበት፥ ቴዎድሮስ በሰፈረበት በየጫካው ስትዘዋወር ነው። ቀደም ሲል ያየችው ትልቅ የሕዝብ መኖሪያ ሠፈር ቢኖር፥ የጭልጋና የመተማ መንደሮች ነበሩ። እነርሱም በጊዜው አስደንቀዋት ነበር። የደረስጌ ጦርነት እንዳበቃ፥ ገብርዬ ቋራ ድረስ ገሥግሦ በመምጣት ጎንደር ይዙዋት ሲገባ ዐይንዋን ማመን አቃታት። ግንቦቹ፥ ሕንፃዎቹ በሰው እጅ የተሠሩ አልመስላት አለ። ራስዋ የለበሰችው ጥበብ ኩታና ቀሚስ የማያሳጣ ቢሆንም ከጎንደር ወይዛዝርት አለባበስ፥ ሹሩባ አሰራሩ፥ ጉትቻው፥ መስቀሉ፥ ሌላው ጌጣ ጌጥ ሁሉ ትንግርት ሆነባት። የካህናቱ ጥምጥም ሳይቀር ሌላ ነው። … ድንገት ከሰው መንደር ገብቶ እንደ ተደናገረ የዱር አውሬ አንዳች ዐይነት ፍርሃት ቢጤ ተሰማት።
“
| — |
የታንጉት ምስጢር | ከብርሃኑ ዘርይሁን | 1979 ታተመ | ገጽ 7
|