ከመጻሕፍት ዓለም (Ethio Books World)

ፈጥኖ የብራና ጥቅሉን ተረተረው። የቆየና የነተበ የብራና ጽሑፍ ነው። በቁም ጽሑፍ በጥንቃቄ የብራናው ወረቀት ላይ የሰፈረውን ነገር ሲያይ ግራ ተጋባ። ይህ ሁሉ ጥንቃቄ የተደረገለትና በጥቅል ብራና የተጻፈው አንድ የሚያውቀው ነገር ነው። እንዲያውም ይህ ጽሑፍ የተወሰደው በህይወት ዘመኑ ከሰበሰባቸው መጻሕፍት መካከል ከአንዱ ውስጥ ነው። ከኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ከሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን ግጥሞች ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ውስጡ እንደ ነበልባል የሚጋረፍበት ግጥም ውስጥ ምን ምስጢር ቢኖር ነው በዚህ በጊታር የድምፅ ሳጥን ውስጥ በተራቀቀ ምስጢር የተላከለት? በጉጉት “ሰቆቃወ ጴጥሮስ” የሚለውንና በጊታሩ በምስጢር ከማያውቀው ቦታ የተላከለትን ግጥሞ ደጋግሞ አነበበው።

ከግጥሙ ሥር እድሜ ልኩን ምስጢር ሆኖበት የኖረውና በ “ቶ” ቅርጽ የተሠራው ባለጉጥ መስቀል ተስሏል። በባለጉጡ መስቀል ላይም ግራ ሲያጋቡት የኖሩት ቃላትና ቁጥሮች ተቀርፀውበታል። 54(4) 9(5) 10(6) 29(23) 77(5) 30(456) 52(7) 33(2) ፬፬፬ 97(5) .. ኦርያ ኢትዮጵያ 98(123) 9(6) 10(67) 40(567) 88(123456) …፬፬፬…መራራ ክንፍ…ማሔር ሻላል ሐሽ ባዝ…ቀጠሮ ቃል…፬፬፬…ዴርቶጋዳ።

ዴርቶጋዳ | ከይስማዕከ ወርቁ | ታተመ 2001 | ገጽ 98