ከመጻሕፍት ዓለም (Ethio Books World)

ሳይሞሉ መጉደል!

ገና ዛሬ አየሁኝ።
ቃልና ገጣሚ ተኳርፈው ሲተኙ
ከሞት ጋር አድሞ አልስቅ ሲል ስንኙ።
ህይወት ቱቢት አስራሽ
ሞት እንደዛብ ልጓም
ነብስሽን ጎንጉኖ
ግ … ጥም አርጎሽ ሲውል
እንግዲህ ምን ልበል?
ላገር ማልቀስ በቀር
አብሮ መግጠም በቀር
አብሮ መሞት አልችል!!
አልለመድኩ አልለመድሽ
እንዲህ ያለ ባሕል!
ወይ ሳይፅፉ መፃፍ
ወይ ሳይሞሉ መጉደል?!

(ለፊርማዬ አለሙ)

በነቢይ መኮንን

እፍታ (100 ትረካዎች፥ ቅፅ አምስት) | አርታኢ እና አዘጋጅ ተስፋዬ ገብረአብ | ታተመ 1993 | ገጽ 295-296 

አንዴ ስመጥሩ ነው ተብሎ ወደሚነገርለት ላውንደሪ 5 ሸሚዞች ወስጄ ሰጠሁ። ሸሚዞቹ ውድና አንዴም ያልታጠቡ ነበሩ። በቀጠሮው ቀን ስሄድ አራቱ ሸሚዞች መጥፋታቸውን ተነገረኝ። ምን እንደሚበጀኝ ብጠይቅ፣ “የማሳጠቢያው አስር እጥፍ ይከፈልሃል” ተባልኩ። 7.50 መሆኑ ነው። ሌላ ምርጫ ስለሌለኝ እሱኑ ለመቀበል ብስማማም፣ “ባለቤቱ ለጥቂት ወጣ አሉ። ጉዳዩን የምታውቀው ሰራተኛ ወልዳ ተኝታለች፣ ለጊዜው ቲኬቱን ለማግኘት አልቻልንም።” በማለት ሲያመላልሱኝ ከርመው እግሬ ስለቀጠነ ሸሚዞቼ ቀልጠው ቀሩ።

የደረቅ እጥበት ጣጣ
ከእሸቱ ተፈራ

እፍታ (መቶ ትረካዎች፥ ቅፅ አምስት) | አዘጋጅና አርታኢ ተስፋዬ ገብረአብ | 1993 ታተመ | ገጽ 422-423

ማሞ ቂሎ

“ተማር ልጄ” ሲሉት አይሰማም አይሰማም
“ሥራ ልጄ” ሲሉት አይሰማም አይሰማም
ያርባ አመቱ ህጻን ካልመቱት አይሰማም
ካልመቱት አይሰማም ካልቆነጠጡት
ወይ ካላስፈራሩት በቃላት አለንጋ በቃላት ብትር
ሥራውን አይሰራ ትምህርት አይማር።

እድሜው ረጅም ነው ሰላሳ አርባ ሃምሳ
ልምድ ያላስተማረው ያምሮ ኮሳሳ
ሥራውን አይሰራ
ወሬ እየፈተለ
ወሬ እያደራ።

ታይፑ አይመታ
ጭቃው አይቦካ
መንገዱ አይሰራ
በልግም ለገማ።

ፊርማው አይፈረም
ሒሳብ አይቆረጥ
ቤቱ አይጠረግ
በኪስ ኪስ ተብሎ
ኪሱ ሳይታሸግ።

ህጻን ያርባ አመቱ ሥራውን አይሰራ
ካላስደነገጡት በቃላት አለንጋ
በብትር ባርጩሜ ባርጩሜ ባለንጋ።

አያ ጎሽሜ | ከፈቃደ አዘዘ | 1973

እፍታ | ቅጽ አመስት (መቶ  ትረካዎች) | አዘጋጅና አርታኢ ተስፋዬ ገብረአብ | ታተመ 1993